የኀብረት ስምምነት ድርድር መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ
ግንቦት 2 ቀን 2009 ዓ.ም.
![]() |
ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሲኢኦ መመሪያ ሲሰጡ |
የአንሊሚትድ ፓኬጂንግ ኃ.የተ.የግ.ማኀበር ማኔጅመንት እና የሠራተኛ ማኀበር ለመጀመሪያ ጊዜ በመሃከላቸው የኀብረት ስምምነት ድርድር እንዲያካሄዱ በመቻሬ ኮርፓሬት ሴንተር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሚያዚያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ፡፡
በዚሁ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር ባደረጉት ንግግር የቴክኖሎጂ ግሩፑ ኩባንያዎች ሠራተኞች መሠረታዊ መብቶችና ጥቅሞች እንዲከበሩ ቴክኖሎጂ ግሩፑ የተለያዩ ፓሊሲዎች ያሉት መሆኑንና ሠራተኞችም በፍላጐታቸውና በነፃነት በማኀበር እንዲደራጁና የኀብረት ስምምነት ድርድር እንዲያደርጉ የሚበረታቱና አስፈላጊው ድጋፍም እንደሚደረግላቸው ጠቅሰው፣ በአሁኑ ጊዜ በቴክኖሎጂ ግሩፑ አሥር ያህል የሠራተኛ ማኀበራት ተቋቁመው ከሚመለከተው የመንግሥት አካል እውቅና አግኝተው የየራሳቸው የኀብረት ስምምነት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኀብረት ስምምነት ድርድር ለማድረግ ፍላጐታቸውን ላሳዩት የአንሊሚትድ ፓኬጂንግ ኩባንያ ማኔጅመንትና የሠራተኛ ማኀበር ድርድሩን በቀና መንፈስና ተጨባጭ ሁኔታን ባገናዘበ አኳኋን እንዲያካሄዱ በማሳሰብ እገዛ ሲያስፈልግ ተገቢው ድጋፍ እንደሚደረግ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር ገልጸዋል፡፡ ለድርድሩ የቀረቡት የኩባንያው ማኔጅመንት እና የሠራተኛው ማኀበር አመራር አባላትም በየተራ ባደረጉት ንግግር ድርድር ማድረጉ የመጀመሪያቸው መሆኑን በመጥቀስ በዚህ ረገድ የቴክኖሎጂ ግሩፑን ልምድ በመከተል ድርድሩን በጋራ ስምምነት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚያጠናቅቁ እምነታቸው መሆኑንና ኩባንያቸውም የቴክኖሎጂ ግሩፑ አባል በመሆኑ ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በኀብረት ስምምነቱ ድርድር መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የሥራ ኃላፊዎችና የሠራተኛ ማኀበር አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
አንሊሚትድ ፓኬጂንግ ኃ.የተ.የግ.ማኀበር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ባለቤትና ሊቀመንበር በሰጡት መመሪያ መሠረት የቴክኖሎጂ ግሩፑን የተቀላቀለ ኩባንያ መሆኑ ይታወቃል፡፡