ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጎ የገነባውን ትምህርት ቤት ለሬጂ ቀበሌ መስተዳደር አስረከበ
ጳጉሜን 5 ቀን 2007 ዓ.ም.
![]() |
የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች አባል የሆነው ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት በኦሮሚያ ክልል፣ በኦዶ ሻኪሶ ወረዳ ለሚገኘው ለሬጂ ቀበሌ መስተዳድር የገነባውን የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ሳይክል ትምህርት ቤት ነሐሴ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ለቀበሌው መስተዳድር አስረክቧል፡፡
የተገነባው ባለ አንድ ፎቅ ሕንጻ፣ በአማካይ 40 ተማሪዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው 10 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ነው፡፡ እያንዳንዱ የመማሪያ ክፍልም በተለይ ለተማሪዎች የተዘጋጁ ባለማስደገፊያ ወንበሮች፣ የመማሪያ ሠሌዳዎች፣ ለአስተማሪዎች የሚሆኑ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች እንዲሁም የመማሪያ ሠሌዳዎች የተሟሉላቸው ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ 16 ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶችን አካቷል፡፡
የሕንጻው ግንባታ ወጪ ሙሉ በሙሉ የተሸፈነው በሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ ሲሆን፣ ግንባታው የተከናወነው እና በእያንዳንዱ ክፍል ውስጥ የሚገኙትን ቁሳቁሶች በሙሉ የተሟሉት እህት ኩባንያዎች በሆኑት በሁዳ ሪል እስቴት እና በዋንዛ ፈርኒሺንግስ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ በትምህርት ቤቱ የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ላይ የጎጂ ዞን የኦዶ ሻኪሶ ወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሻኪሶና የሬጂ ቀበሌ ነዋሪዎች፣ የኩባንያዎች ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የኩባንያው የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አያሌው ተበጀ በአደረጉት ንግግር፣ የሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ በአካባቢው መኖር በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ችግር በቅርብ ለመረዳትና በራሱ ተነሳሽነት ለአካባቢው ልማትና ዕድገት ዘርፈ ብዙ በሆነ መልኩ ማለትም፣ በትምህርት፣ በውሃ፣ በመንገድ፣ በጤና እና በመሳሰሉት መስኮች ድጋፍ ለማድረግ አስችሎታል ብለዋል፡፡
የኦዶ ሻኪሶ ወረዳ አስተዳደሪ አቶ ኤጀረሳ ቴዴቻ በበኩላቸው፣ የሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ፣ በወረዳችንም ሆነ በዞናችን በምናደርጋቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ሁሉ መጠነ ሰፊ የሆነ ተሣትፎ እያደረገ የሚገኝ ኩባንያ በመሆኑ እንደ ልማት ምንጫችን ልንጠብቀው እንደ ልማት አጋራችን ልናየው ይገባናል ብለዋል፡፡
የሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር የሆኑት ዶ/ር አረጋ ይርዳው ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግር፣ ሼክ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አል-አሙዲ ለአገራችን ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ የሚገኙ፣ ለሕዝብ አገልግሎትና ጠቀሜታ እስከዋለ ድረስ ገንዘብ ለምን ወጣ? ምን ተደረገበት? የት ደረሰ? የማይሉ፣ በአግባቡ የሚቀርብላቸውን በልብ ቀናነት የሚፈቅዱ፣ አገር ወዳድ፣ በጣም ፍፁም የሆኑ አገራቸውንና ወገናቸውን የሚወዱ ደግና ለጋስ ሰው ናቸው ብለዋል፡፡ አያይዘውም እኛም በዚህ አካባቢ ከምናደርጋቸው ልዩ ልዩ የልማት ድጋፎች መካከል የተለየ ትኩረት የምንሰጠው ለትምህርት ነው፡፡ ምክንያቱም ትምህርት ሰውን በደንብ አድርጎ የሚያንፅ፣ አድሎ የማይፈጥር፣ ለማመዛዘን የሚያስችል አቅም የሚሰጥ፣ ትልቅ መሣሪያ እና ሰዎች የትም ቦታ ቢሄዱ የማያፍሩበት ሀብት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
በማስከተልም ከዚህ አካባቢ ከሚወጡ ልጆች እና እዚህ ት/ቤት ከሚማሩ ወጣቶች መካከል ማንኛው የአገር መሪ፣ የትኛው ሐኪም፣ የቱ ፓይለት እንደሚሆኑ ማወቅ አንችልም፡፡ ስለዚህ ልጆቻችሁን ሁሉ ማስተማር ይኖርባችኋል፡፡ ቀጣዩ የኩባንያችን ሥራ የሚሆነው ለትምህርት የምንሰጠውን ድጋፍ በማጠናከር ለትምህርት ቤቱ የአስተዳደር ቢሮ፣ ቤተ መጻሕፍት (Library) መገንባትና በመጻሕፍት ማደራጀት ይሆናል፡፡
በሥነ-ሥርዓቱ መጨረሻ ላይም እንግዶቹ ሕንፃውን ከጎበኙ በኋላ የሀገር ሽማግሌዎች ምረቃት እንዳበቃ፣ ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሕንፃውን ቁልፍ ለኦዶ ሻኪሶ ወረዳ አስተዳደሪ ለአቶ ኤጀረሳ ቴዴቻ እና ለቀበሌው ተወካይ ለአቶ በቀለ ኡርጌሣ አስረክበዋል፡፡