ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ሦስተኛውን የከፍተኛ ደረጃ የወርቅ ማምረት የሥራ ውል ተፈራረመ
ጥር 24 ቀን 2009 ዓ.ም.
የሥራ ውሉ ስምምነት ፊርማ ሲካሄድ |
በማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር እና በሚድርክ ወርቅ ማዕድን ኃ.የተ.የግል ማህበር መካከል ጥር 22 ቀን 2009 ዓ.ም በሚኒስቴሩ መ/ቤት በተከናወነው ሥነ-ሥርዓት ላይ የከፍተኛ ደረጃ የማዕድን ማምረት ውል ተፈርሟል፡፡
የማዕድን ቦታው የሚገኘው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መተከል ዞን በቡለን ወረዳ ጐንጐ ቀበሌ ሲሆን በ27.2 ስኩየር ኪሎ ሜትር ላይ ያረፈ ነው፡፡
ውሉን በፊርማቸው ያጸደቁት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሚኒስትር ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ እና የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር እና የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር ዶ/ር አረጋ ይርዳው ናቸው፡፡ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ገብረ እግዚአብሔር የማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በፊርማው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙ ከፍተኛ ኃላፊዎች |
ለወርቅ ማምረቱ ውል ተፈጻሚነት በቅድሚያ የመሠረት ልማት አውታሮች በተለይም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና የመንገድ ሥራ ግንባታ መሟላት እንዳለባቸው ሁለቱም ወገኖች አስምረውበታል፡፡
የማዕድን ምርመራ ሥራው ከአሥራ አንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን ከብር 310 ሚሊዮን በላይ ወጥቶበታል፡፡ የወርቅ ማምረቱ ተግባር ለብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕድገትና ለብዙ ዜጐች የሥራ ዕድል በመፍጠር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡